የእግዚአብሔር ቤት

እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ መልቶ የሚኖር አምላክ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ‹‹ምሉዕ በኩለሄ›› ይባላል፡፡ ይኽም በሁሉም ቦታ ያለ፣ የሚገኝ ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ፈጣሪ ስሙ እንዲጠራበትና እንዲመሰገንበት ወዶ የሚመርጠው ቦታ ደግሞ አለ፡፡ በዚያም ስፍራ በፈቃደ እግዚአብሔር ተገቢው ሥርዓት ይፈጸምና ቤት ይታነጻል፡፡ ያም ቤት ‹‹የእግዚአብሔር ቤት›› ይባላል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ›› ብሏል፡፡ (መዝ121.1)
ክርስቲያኖች በጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የተወለዱ ስለሆነ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፡፡ ልጆች ደግሞ በአባታቸው ቤት የሚኖሩ ሲሆን የአባታቸውም ቤት ቤታቸው ነው፡፡ ‹‹በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን?›› እንዲል፡፡ (ሉቃ2.49) የእግዚአብሔር ቤት የክርስቲያኖች ቤት ወይም ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› የሚባለው ስለዚህ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስሟ እንደሚያመለክተው የክርስቲያኖች ሁሉ ‹‹ቤት›› ናት፡፡ ይህም ከጸሎት ቤትነቷ ባሻገር ሰፋ ያለ ትርጉምና ምሥጢር ያላት ናት ማለት ነው፡፡ ‹‹መስጊድ›› ከመስገጃነት ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ ‹‹የጸሎት ቤትም›› ከጸሎት ቤትነት ያለፈ ምሥጢር አናገኝበትም፡፡ ‹‹ቤተ እግዚአብሔር፤ ቤተ ክርስቲያን›› ባልን ጊዜ ግን በውስጧ መጸለያችንና መስገዳችን እንደተጠበቀ ሆኖ ፍጹም የኔነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ ስያሜ ነው፡፡
ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ስሟ ብቻ እንኳን ብዙ የሚመስጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰው በቤቱ እንደሚኖር በቤተ ክርስቲያን እንኖራለን፤ እንደሚመገብ የነፍስ ምግብ እንመገባለን፤ እንደሚያርፍ ዕረፍተ ነፍስና ዕረፍተ ሕሊና እናገኛለን፤ እንደሚተጣጠብና እንደሚናጻ እኛም በቤተ ክርስቲያን ቃሉን ሰምተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ሥጋ ወደሙን ተቀብለን ከኃጢአት እንነጻለን፤ ሰው በቤቱ ከወላጆቹና ከቤተሰቡ ጋር ተገናኝቶ እንደሚነጋገር እኛም ከፈጣሪያችንና ከቅዱሳን፣ ከመላእክትና ከምእመናን ቤተሰቦቻችን ሁሉ ጋር በመንፈስ ተሰባስበን እንገናኛለን፡፡
ከሥጋ ተፈጥሮ የነፍስ ተፈጥሮ እንደሚበልጥ ከቤታችንም የነፍስ ቤታችን ቤተ ክርስቲያን ትበልጣለች፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው ቤተ እግዚአብሔር ሰው ከፈጣሪው ጋር የሚገናኝባት ‹‹የሰማይ ደጅ›› ናት፡፡ (ዘፈፍ28.17) በሰዓቱ ወደ ቤቱ የማይገባ ወይም የሚያመሽ፣ ያለ በቂ ምክንያት ከቤቱ ውጭ የሚያድር ወይም ደስ ሲለው ብቻ ቤቱን የሚያስብ ልጅ ምን ይባላል? ክርስቲያን ተብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን የማይሄድ ሰውም የሚታየው እንዲሁ ነው፡፡
ክርስቲያን ነጋ ጠባ ወደ ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ይኖርበታል፡፡ በልቡም ከቤተ ክርስቲያን መራቅ ይጎዳዋል፡፡ መዝገባችን ባለበት በዚያ ልባችን እንደሚኖር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ (ሉቃ12.34) ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የሕይወት መዝገባችንንና መንፈሳዊ ሀብታቸን ሁሉ የተቀመጠባት ስፍራ ናት፡፡ ስለዚህ ሠለስቱ ምእት በሃይማኖተ አበው ‹‹አሌሊ ገይሠ ኀበ ቤተ ክርስቲያን›› እንዳሉ ነገ ዛሬ ሳንል ‹‹በማለዳ ወደ ቤተ ክርስቲያን›› መገስገስ ይኖርብናል፡፡ (ሃይ.አበ ዘሠ.ምእት)
ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለ መሄድ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ (መዝ121.1) በእውነትም ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያስደስታል፡፡ ወንድሞች በኅብረት በሚቀመጡበት በዚያ ‹‹እግዚአብሔር በረከትን ሕይወትንም እስከዘላለሙ ድረስ አዟልና፡፡›› (መዝ132.3)
ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሲሄዱ ደስ የሚያሰኘው ደግሞ የሕንፃው አሠራርና ውበት ሳይሆን በቤተ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለሚገኝ ነው፡፡ እውነተኛ ደስታ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው እንጂ በማግኘትና በማጣት ወይም በማየትና በሥጋዊ ነገሮች ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎችን ሲዘረዝር ‹‹ደስታ››ን አንድ ብሎ ጠቅሶታል፡፡ (ገላ5.22) ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ወዳደረባት ቤተ ክርስቲያን መሄድ ሰላምና ደስታን ይሰጣል፡፡
ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድህና ውሳጣዊ ሰላም በማግኘትህ የምትጠቀመው ራስህ ነህና እግርህን አንሥቶ ላለመሄድ ምክንያት አታብዛ፡፡ ሌሎች እንዲወተውቱህና እንዲለማመጡህም አትፈልግ፡፡ ሥራና ኃላፊነት እንደተደራረበብህም አትናገር፡፡ በዚህ ዓለም ሰው ከፈጣሪው የሚበልጥ ጉዳይ እንደሌለው ዕወቅ፡፡ ጉዳዬ የምትላቸው ማናቸውም ነገሮች በሞት የሚገቱና ሳትወድ በግድ የምትተዋቸው ናቸው፡፡ ፈጣሪህ በሞት ሲጠራህ ጉዳይ አለብኝ ትለዋለህን? ወይስ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ሁሉ ያንተን ያህል ሥራና ጉዳይ የሌላቸው ቦዘኔ ናቸውን? እንዲህ ማሰብህ በቤተ ክርስቲያን የሚተጉትን ሰዎች እንደመዝለፍ ሊቆጠርብህ ይችላል፡፡ ካንተ በበለጠ ሥራና ኃላፊነት ተጠምደው ቤተ ክርስቲያን የሚመላለሱ ሰዎች በርካታ ናቸውና መፋረጃ ይሆኑብሃል፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄደ አስፈላጊውን ነገር ለማከናወን ጊዜህን ካሁኑ አመቻች፡፡
በዚህ ዓለም እንዲኖርህ የምትፈልገውና የምትደክምለት ማንኛውም ነገር የምኞትህን ያህል አስደሳች የሚሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲጨመርበት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዳ ‹‹ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?›› ይልሃል፡፡ (መክ2.25) ስለዚህ ፈጣሪህን ትተህ ደስታን አትሻ፤ አታገኛትምና፡፡ ‹‹ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ›› የተባለው ክፉ ትንቢት ባንተ እንዳይፈጸም ትጋ፡፡ (2ጢሞ3.4)
ወደ ቤተ እግዚአብሔር ቤት መሄድ እየፈለጉ ከዓቅም በላይ በሆነ ምክንያት ያልቻሉ አሉ፡፡ አንዳንዶች በቤተሰብም ይሁን በኢአማንያን ይህን መብት ያላገኙ ናቸው፡፡ ሌሎች በአካባቢያቸው ቤተ ክርስርስቲያን ባለመኖሩ ነው፡፡ ይህን ከአገር ቤት የወጣ ሰው የበለጠ ይረዳዋል፡፡ ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያን ይሄድ የነበረ ሰው ይህን የመሰለ ችግር ቢያጋጥመው ቤተ ክርስቲያንን መናፈቁ እንኳን ከመሄድ ሊቆጠርለት ይችላል፡፡ ችግሩ ከአቅሙ በላይ ነውና፡፡ ነገር ግን በቅርቡ እያለ ያልተሳለመ ሰው ምን ምክንያት ያቀርባል?
ቅዱስ ዳዊት ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ሀብታም ንጉሥም ነበር፡፡ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ የወደደውን ለማድረግ የሚያስችለው የተሟላ ቤት ነበረው፡፡ በሥጋ ስንመለከተው ከፈጣሪ ቤት የሰዎች ቤት ደምቆና አምሮ የሚታይበት ጊዜ አለ፡፡ (ሐጌ1.4) ለምሳሌ፡-ቅዱስ ዳዊት ከእግዚእብሔር ቤት ይልቅ ለዓይነ ሥጋ የሚያምርና የተዋበ ቤት ነበረው፡፡ ይህም ቤቱን ከቤተ እግዚአብሔር ጋር አወዳድሮ የእርሱ በልጦ ስላገኘው ለፈጣሪው የተሻለ ቤት ለመሥራት በመፈለጉ ይታወቃል፡፡ (2ሳሙ7.2) ይሁን እንጂ እርሱን የሚያስደስተው ራሱ እንደነገረን ‹‹ወደ እግዚአብሔር ቤት›› መሄድ ነው፡፡ ለምን ይመስልሃል?
ከንጉሥ ዳዊት በላይ ኃላፊነትና የሥራ ጫና ያለብህ ይመስልሃል? እርሱ በዚያ ሁሉ ኃላፊነት ላይ ቤተ እግዚአብሔር መሄድ ያስደስተው ነበር፡፡ አንተስ? የሥራ መብዛትና መሔድ አለመፈለግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ሥራ ይበዛብኛል ካልክ መሄድ ግን እፈልግ ነበር እያልክ ነው፡፡ በእርግጥ አንተን ወደ ኋላ የሚስብህ የሥራ መደራረብ ብቻ ይመስልሃል? ከሆነ ከሰዎች ጋር ሻይ፣ ቡና ለመጠጣትና ለመዝናናትም ጊዜ የለህም? ፊልምና ቴአትር ቤት አትሄድም?
ምእመናን! በዋናና በልዩ ልዩ ስፖርት፣ በ‹‹ባዝና በሳውና›› ፣ በጸጉር ሥራና በ‹‹ፓርቲ››፣ በ‹‹ጌት ቱጌዘር››፣ ‹‹ቻት በማድረግ››፣ ‹‹ፑል›› በመጫወት፣ ‹‹በካዚኖ››፣ በ‹‹ኮምፒውተር ጌሞች›› እና በሌሎችም ነገሮች የምታጠፏቸውን ጊዜያት እስኪ መለስ ብላችሁ አስቧቸው፡፡ እንዲሁ የሚባክኑትስ? ታዲያ ጊዜ የማይኖረን ወደ ቤተ እግዚአብሔር ለመሔድ ሲሆን ብቻ ነው? ከዚህ ሁሉ ትዝብት ሰዎች ብዙ ጊዜ ቤተ እግዚአብሔር ከመሔድ የሚሰንፉት ጊዜ አጥተው ሳይሆን ለነፍሳቸው ግምት ስለማይሰጧትና እምነት ስለሚጎድላቸው ነው፡፡ ለመንፈሳዊ ነገር ያላቸው ፍቅር ሲቀዘቅዝና ነፍሳቸው ስትዝልም ይህ ችግር ይከሰትባቸዋል፡፡ ነገር ግን ድክመታቸውን አምኖ ከማረም ይልቅ ጊዜ በማጣት ያሳብባሉ፡፡
ቤተ እግዚአብሔር መሄድ በፕሮግራም የሚደረግ ነው እንጂ ጊዜን ማጥፋት አይደለም፡፡ የሰንበት ቀን የእግዚአብሔር ቀን ነው፡፡ ከዕለታትም የጸሎትና የትምህርተ ወንጌል ጊዜ በመመደብ ጊዜያችንን ማስባረክ ይገባናል፡፡ ለእግዚአብሔር ከመስጠት የሰሰትነው ጊዜ ባልገባን መንገድ ይባክናል፡፡ ለእግዚአብሔር ከጊዜ ዐሥራት ብናወጣ ግን የተረፈንን ጊዜ አስባረክን ማለት ነው፡፡ ለምንሻውም ጉዳይ ይብቃቃልናል፡፡
ይህ ጊዜ በተለይ ሰዎች ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገጻቸውን መመለስ እንዳለባቸው የሚጠቁም ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ›› በማለት በተናገረ ጊዜ ብዙ ነገር አመልክቶናል፡፡ (መዝ121.1) አንደኛ በርካታ ሰዎች ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንሂድ ይሉት እንደነበር ያሳየናል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን እንዲሔዱ መጋበዝ የመምህራንና የካህናት ወይም የንስሐ አባቶች ድርሻ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ክርስቲያን ኃላፊነት መሆኑን ይጠቁመናል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እነርሱ ‹‹ሳያዝኑለት››ና ሥራ ይበዛበታል ሳይሉ ‹‹እንሂድ›› ብለው ሲጋብዙት እርሱም በበኩሉ ደስተኛነቱን ገለጠ፡፡ እንዲህ ዓይነት ቀና መልስ የሚጠሩንንና መንፈሳዊ ነገር የሚጋብዙንን ሰዎች ምን ያህል እንደሚያበረታታቸው መመልከት አለብን፡፡ ስለዚህ የነገ ዕድላችንን እንዳንዘጋ ስንጠራ በደስታ እሺ ማለትን አንዘንጋ፡፡
እንደ ቅዱስ ዳዊት ‹‹በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ›› ብሎ እግዚአብሔርን አንዲት ነገር የሚለምን ሰው በእውነት ብፁዕ ነው፡፡ (መዝ26.4) ቅዱስ ዳዊት ልመናው በቤተ እግዚአብሔር መከበርና መቀመጥ ሳይሆን እንደ ተራ ሰው መናቅ፣ መጣልና መዋረድ ነበር፡፡ በዓለም ከመከበር በቤተ ክርስቲያን መዋረድ ይበልጣል፡፡ በጠላት ከመሳም በወዳጅ መነከስ ይሻላል፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ዳዊት ‹‹በኃጥአን ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ በእግዚአብሔር ቤት ብጣል መረጥኩ›› አለ፡፡ (መዝ83.0) ስለዚህ ክብራችን ወይም ክብር መፈለጋችን ከቤተ እግዚአብሔር እንዳያርቀን እንጠንቀቅ!! ኑሮአችን ሲሻሻልና ክብር ሲበዛልን ከቤ እግዚአብሔር የምንጠፋ ብዙዎች ነንና፡፡ አምላካችን በቅዱስ ዳዊት ታሪክ ይዋቀሰናልና ወደ እርሱ አሁኑኑ እንመለስ፡፡
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አዘጋጅ ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ